ባለፉት ስምንት ወራት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዲጂታል የባንክ አገልግሎቶች ከ10 ትሪሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር ተካሄደ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሪዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደገለፁት ባለፉት ስምንት ወራት በባንኩ ዲጂታል አገልግሎቶች በተከናወኑ ከ800 ሚሊዮን በላይ ግብይቶች ከ10 ትሪሊዮን በላይ የገንዘብ ዝውውር ተፈፅሟል፡፡ ይህም ከአጠቃላዩ የገንዘብ ዝውውር 73 በመቶ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ባንኩ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ባንክ ለመሆን በሚያደርገው እንቅስቃሴ በአሁኑ ጊዜ የለውጥ ሥራ ላይ መሆኑን የገለፁት አቶ አቤ፣ ዲጂታል የባንክ አገልግሎቶችን ወደላቀ ደረጃ ማድረስ ደግሞ የለውጡ ሥራ አንዱ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አቶ አቤ 32 ሚሊዮን የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች በባንኩ እንዳሉ እና በየቀኑ 4 ሚሊዮን ደንበኞች በዲጂታል አገልግሎት እንደሚስተናገዱ ገልፀዋል፡፡ የባንኩን ዲጂታል አገልግሎቶች ደህንነት አስተማማኝ ለማድረግ ጠንካራ የሳይበር ደህንነት ስርዓት መዘርጋቱን የገለፁት አቶ አቤ፣ በአሁኑ ጊዜ የባንኩ የመረጃ ደህንነት ሥራ አመራር እጅግ ዘመናዊ፣ በስርዓት የሚመራ እና በቴክኖሎጂ እና በብቁ ባለሙያዎች የተደገፈ በመሆኑ በሀገራችን ላሉ ለሁሉም የፋይናንስ እና ሌሎች ተቋማት እንደማሳያ የሚሆን ቁመና ያለው መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል፡፡ በዚህም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት በተለያዩ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች የደህነነት ማረጋገጫ እውቅና እንዳገኘ አስረድተዋል፡፡