የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሳይበር ጥቃት እንዳልደረሰበት ተገለፀ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም በቅርንጫፍ እና በዲጂታል የባንክ አገልግልቶቹ ላይ ለተወሰኑ ሰዓታት የአገልግሎት መቋረጥ ማጋጠሙ ይታወቃል፡፡ ይህን በማስመልከት በዛሬው እለት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ባንኩ ምንም አይነት የሳይበር ጥቃት እንዳልደረሰበት ገልፀዋል፡፡ ባንኩ ላይ የተለያዩ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች በየጊዜው እንደሚደረጉ እና ባንኩ ባለው እጅግ ጠንካራ የሳይበር ደህንነት ስርዓት እንደሚመከቱ የገልፁት አቶ አቤ አሁን የተፈጠረው ችግር በሲቢኢ ብር እና በሞባይል ባንኪንግ አገልግሎቶች ላይ ተደርጎ በነበረ አዲስ የሲስተም ማሻሻያ ትግበራ ክፍተት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ባንኩ የዲጂታል አገልግሎቶቹን ይበልጥ በማዘመን እና ለደንበኞች ይበልጥ ምቹ ለማድረግ በየጊዜው ማሻሻያዎችን ይተገብራል ያሉት አቶ አቤ፣ አሁን የተፈጠረውን ችግር በማጣራት ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አቶ አቤ በቅርንጫፎች እና በዲጂታል የባንኩ አገልግሎቶች ላይ መቋረጥ የገጠመው ሲስተሙ አልሠራ ባለማለቱ ሳይሆን፣ አዲስ ተግባራዊ ተደርጎ በነበረው የሲስተም ማሻሻያ ሳቢያ በተፈጠረ ክፍተት የተደረጉ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውሮችን በመለየት ለማገድ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሳይበር ደህንነት በተለያዩ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች የደህነነት ማረጋገጫ እንዳገኘ አቶ አቤ ገልፀው፣ በዚህ ረገድ ደንበኞች ስጋት ሊገባቸው እንደማይገባ አረጋግጠዋል፡፡