የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢሬቻ ክብረ በዓል ስፖንሰር በመሆኑ የተሰማውን ታላቅ ደስታ ገለፀ፡፡

ይህ የተገለፀው ባንኩ በፕላቲኒየም ደረጃ ስፖንሰር ያደረገው የኢሬቻ ክብረ በዓል አካል በሆነውና በስካይላይት ሆቴል በተከናወነው 2ኛው የቱሪዝም ሽልማት እና የሚስ ቱሪዝም ኦሮሚያ የቁንጅና ውድድር ዝግጅት ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሱራ ሳቀታ በዝግጅቱ ላይ እንደገለፁት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኦሮሞ ሕዝብ ታላቅ የምስጋና በዓል የሆነው ኢሬቻ የ2015 ዓ.ም ክብረ በዓል አካል በመሆኑ ታላቅ ክብር ተሰምቶታል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ዓለም ሊወስዳቸው የሚገቡ ትልልቅ ተሞክሮዎች እና ለረጅም ጊዜ ሲተገብራቸው የቆዩ በርካታ ከተፈጥሮ እና ከፈጣሪ ፈቃድ ጋር የተስማሙ ባህሎች እና እሴቶች ባለቤት የሆነ ሕዝብ መሆኑን አቶ ሱራ ተናግረዋል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ያሉትን እንደገዳ ሥርዓት እና ኢሬቻ የመሳሰሉ የማይዳሰሱ እና ሌሎች የሚዳሰሱ የቱሪስት መስህቦችን በማልማት የክልሉ ህዝብ እና የሀገራችንን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት አካል ለመሆን ባንኩ ዝግጁ መሆኑን አቶ ሱራ አረጋግጠዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገልግሎቱን ካስፋፋባቸው አካባቢዎች መካከል የኦሮሚያ ክልል አንዱ መሆኑንም የገለፁት አቶ ሱራ ፣ ህዝቡና መንግስትም የባንኩን አግልግሎቶች በመጠቀም ከባንኩ ጎን እንዲቆሙ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ አቶ ሱራ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኦሮሚያ ክልል እና የህዝቧ የልማት አጋር ለመሆን በቁርጠኝነት መነሳቱን አረጋግጠው፣ መልካም የኢሬቻ በዓል ተመኝተዋል፡፡ 2ኛው የቱሪዝም ሽልማት እና የሚስ ቱሪዝም ኦሮሚያ የቁንጅና ውድድር ዝግጅት በቱሪዝም ዘርፍ በኦሮሚያ ክልል የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ተቋማት ሽልማት እና እውቅና በመስጠት እንዲሁም በያዝነው አመት የቱሪዝም አምባሳደር ሆና ኦሮሚያን የምታስተዋውቀውን ቆንጆ በመምረጥ ተጠናቋል፡፡