የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ 890.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2014 (2021/22) በጀት ዓመት 154.9 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ የተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ ጠቅላላ የተቀማጭ ገንዘቡን 890.1 ቢሊዮን ብር ማድረሱን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ አስታውቀዋል፡፡ ባንኩ በበጀት ዓመቱ 27 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ትርፍ ያገኘ ሲሆን ይህም ከእቅዱ 16.3 በመቶ፣ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ የ43 ነጥብ 9 በመቶ ብልጫ እንደሚያሳይ አቶ አቤ ገልጸዋል። ባንኩ 179.2 ቢሊዮን ብር ብድር ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች መስጠቱን ያስረዱት አቶ አቤ፣ 120.6 ቢሊዮን ብርም ከተሰጡ ብድሮች መሰብሰብ መቻሉን አስረድተዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በተመለከተ ከተለያዩ ዘርፎች 2.6 ቢሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን፣ በመንግስት ትኩረት ለተሰጣቸው ለተለያዩ የገቢ እቃዎች እና ለሌሎችም 7.7 ቢሊዮን ዶላር ባንኩ መክፈሉንም ነው አቶ አቤ የገለጹት፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠቅላላ ሀብት 1.2 ትሪሊዮን ብር መድረሱንም አቶ አቤ ካቀረቡት ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡ የባንኩን አገልግሎት ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለማዳረስ በሚደረገው ጥረት በበጀት ዓመቱ 124 አዳዲስ ቅርንጫፎች የተከፈቱ ሲሆን፣ የባንኩ አጠቃላይ የቅርንጫፍ ብዛትም 1824 ደርሷል፡፡ የደንበኞችን በቴክኖሎጂ የታገዙ አገልግሎቶች ተጠቃሚነት በማሳደግ የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን ለመቀነስ ባንኩ በሚያደርገው ጥረት በበጀት ዓመቱ ከተከናወኑ የሂሳብ እንቅስቃሴዎች ውስጥ 35 በመቶ የሚሆነው በዲጂታል የባንክ አገልግሎቶች መከናወኑን አቶ አቤ በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ ተጨማሪ 2.9 ሚሊዮን አዳዲስ ሂሳቦች መከፈታቸውነ የገለጹት አቶ አቤ፣ የባንኩ አጠቃላይ የገንዘብ አስቀማጮች ብዛት 35.9 ሚሊዮን መድረሱንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡