የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በግብር ከፋዮች ሽልማት የፕላቲኒየም ደረጃና ልዩ ተሸላሚ ሆነ፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም በብሔራዊ ቤተመንግስት በተካሄደው 6ኛው ዙር የታማኝ ግብር ከፋዮች እውቅና እና ሽልማት መርሐ ግብር ከተሸለሙት 550 ግብር ከፋዮች መካከል አንዱ ሆኗል፡፡ ባንካችን በፕላቲኒየም ደረጃ ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ከተሸለሙት 66 ግብር ከፋዮች አንዱ ሲሆን ከ20 ልዩ ተሸላሚ ግብር ከፋዮችም አንዱ መሆን ችሏል፡፡ 20ዎቹ ልዩ ተሸላሚዎች ባለፉት አራት የሽልማት ፕሮግራሞች ከደረጃቸው ሳይንሸራተቱ በተከታታይ እድገት በማስመዝገብ የፕላቲኒየም ደረጃቸውን ጠብቀው የዘለቁ መሆኑን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ልዩ ተሸላሚዎች ለታክስ ሕጉ ካላቸው የተገዥነት ደረጃ በተጨማሪ በከፈሉት ግብር መጠን ከፍተኛው 27.2 ቢሊዮን ዝቅተኛው ደግሞ 854.4 ሚሊዮን ብር ግብር መክፈላቸውን ሚኒስቴር መ/ቤቱ አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሽልማት መርሐ ግብሩ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የፕላቲኒየም ደረጃ ተሸላሚ ሆኖ የቆየ ሲሆን በዚህኛው ዙር ከፕላቲኒየም በተጨማሪ ልዩ ተሸላሚም ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁሌም የሚተማመኑበት ባንክ !