የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሲቢኢ ኑር ደንበኞች ጋር የውይይት መድረክ አካሄደ፡፡

“ስኬታማ ምዕራፍ፤ ብሩህ ተስፋ” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ የሚገኘው የሲቢኢ ኑር 10ኛ ዓመት ክብረ በዓል አንዱ አካል ሆኖ በተከታታይ የሚካሄደው የደንበኞች ምክክር መድረክ በዛሬው እለት (ህዳር 8፤ 2016) በአዲስ አበባ ከሚገኙ የሲቢኢ ኑር ደንበኞች ጋር በማካሄድ ተጀምሯል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በምክክር መድረኩ ላይ በመገኘት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በሀገራችን የተጀመረበትን ሂደት፣ ባንኩ ከ20 ዓመት በፊት በእምነታቸው ምክንያት ከባንክ የራቁ የህብረተሰብ ክፍሎችን የባንክ ተጠቃሚ ለማድረግ ያደረጋቸውን ጥረቶች እና አሁን ያለበት ደረጃ ለማድረስ ያሳለፈውን ሂደት በሰፊው ያብራሩ ሲሆን፣ መድረኩ ከባንኩ ጋር አብረው ለሚሠሩ ደንበኞች ምስጋና ለማቅረብ እና በቀጣይ የተሻለ ሥራ ለመሥራት የደንበኞችን አስተያየት ለመቀበል መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡ ከባንኩ ጋር የሚሠሩ የሲቢኢ ኑር ደንበኞች ይሻሻሉ፣ ይስተካከሉ ያሏቸውን ጉዳዮች በመድረኩ ያነሱ ሲሆን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ፣ የሲቢኢ ኑር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኑሪ ሁሴን እና የሸሪዓ አማካሪ ኮሚቴ አባል የሆኑትዶ/ር ሞሀመድ ዘይን ኑር ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በመድረኩ ተገኝተው በውይይቱ የተሳተፉ የባንኩ ደንበኞች “እንኳን ለ10ኛ ዓመት የሲቢኢ ኑር ክብረ በዓል አደረሳችሁ” መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ ባንኩ በእምነት ምክንያት ከባንክ የራቁ ደንበኞችን የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ላደረገው ጥረት እና እየሠራ ላለው ጠንካራ ሥራ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በውይይት መድረኩ የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች፣ የባንኩ የሸሪዓ አማካሪ ኮሚቴ አባላት፣ ደንበኞች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡