የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን እና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን የሶስትዮሽ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።

ጥቅምት 14፣ 2017 በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋናው መስሪያ ቤት በተደረገው በዚህ ስምምነት ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አቶ ደረጀ ፉፋ እንደተናገሩት የስምምነቱ ዋና አላማ በትግራይ ክልል በጦርነት ወቅት የተሳተፉ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታትና መልሶ ለማቋቋም የሚውለውን የገንዘብ ዝውውር ለማቀላጠፍ ነው። አቶ ደረጀ ባንኩ የተሰጠው ኃላፊነት ከባንክ ሥራ ባሻገር ሀገራዊ ግዴታንም ለመወጣት የሚደረግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ባንኩ ለሥራው ስኬት ቁርጠኛ መሆኑን የተናገሩት አቶ ደረጀ፣ ያለው ተቋማዊ አቅም፣ የቅርንጫፍ ተደራሽነት እና ብቁ የሠው ኃይል ይህን ማድረግ እንደሚያስችለው አስረድተዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም በኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ዶው እንዳሉት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት የተሳተፉ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታትና መልሶ እንደገና ወደ ሕብረተሰቡ ለመቀላቀል እና ለማቋቋም የተጀመረውን ውጥን ለማሳካት በታቀደው መሰረት ሁሉም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት እንዲሳተፉም ጠይቀዋል። የዚህ የሶስትዮሽ ስምምነት ለዚህ እንደ ማዕዘን ድንጋይ ስለሚቆጠር ሁላችንም በጋራ ለመስራት እና ፕሮግራሙን በተሳካ ሁኔታ ለመተግበር ቃል የገባንበት ነው ብለዋል። የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን በበኩላቸው በትግራይ ክልል በጦርነት ወቅት የተሳተፉ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታትና መልሶ የማቋቋም ስራ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን እና በቅርቡም ስራ እንደሚጀመር ገልፀው፣ የዚህ የሶስትዮሽ ስምምነት መፈረም ስራዎችን በፍጥነት እና በጥራት ለማከናወን ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል። በዚሁ የመግባቢያ ስምምነት ሥነ-ሥርዓት ላይ ከሦስቱም ተቋማት የተገኙ ተወካዮች ተገኝተዋል።