ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ እና የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ስራአስኪያጅ አኑዋር ሱሳ ናቸው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ በስምምነቱ ወቅት እንደተናገሩት ባንኩ በቴሌኮም ዘርፍ አለም አቀፍ ልምድ ካለው ድርጅት ጋር በጋራ ለመስራት እድል በማግኘቱ መደሰታቸውን በመግለፅ ሁለቱ ትላልቅ ድርጅቶች በስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ በመስራት በጋራ ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያረጋግጡ ተናግረዋል። በአገሪቱ በባንክ ኢንዱስትሪ ግንባር ቀደም የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በየጊዜው እያደገ፣ በለውጥ እየኖረ፣ በ80 ዓመታት ጉዞው፣ አጠቃላይ ተቀማጭ ሀብቱ 1.2 ትሪሊዮን ብር፣ የባንኩ የደንበኞች ብዛትም 38.1 ሚሊዮን፤ 1,880 ነላይ ቅርንጫፎች፣ በዲጂታል የታገዘና ደንበኛን ያማከለ የባንክ አገልግሎት እየሰጠ ነው ያሉት አቶ አቤ ከሳፋሪኮም ጋር ያደረገው ስምምነትም አጋዥ እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡ ስምምነቱ ውጤታማ ለማድረግም የዲጂታል አማራጮችን በማስፋት ባንኩ የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚወጣ አቶ አቤ አስገንዝበዋል፡፡ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ስራአስኪያጅ አኑዋር ሱሳ በበኩላቸው ድርጅታቸው ከአንጋፋው የኢትዮጰያ ንግድ ባንክ ጋር ለመስራት መስማማቱን ለሚያከናውናቸው ስራዎች የላቀ አስተዋፅኦ እንዳለው በመግለፅ ለተለይም የሁለቱን ተቋማት ተሞክሮ በመጠቀም አጋርነታቸው እንደሚጠናከር አረጋግጠዋል፡፡ በስምምነቱ ወቅት የሁለቱም ተቋማት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡