የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ለ10 አመት የሚቆይ የ200 ሚሊዮን ብር የስፖንሰርሺፕ ስምምነት በሸራተን አዲስ ሆቴል ተፈራረሙ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ለ10 አመት የሚቆይ የ200 ሚሊዮን ብር የስፖንሰርሺፕ ስምምነት በሸራተን አዲስ ሆቴል ተፈራረሙ፡፡ ========================= ሰኔ 16 ቀን 2014 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል የተፈረመው ስምምነት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነቱን ለማሳደግ የጀመረውን የዘመናዊ ስቱዲዮ ግንባታ በአጋርነት ለመሥራት የሚያስችል ነው፡፡ ሁለቱን አንጋፋ ተቋማት በመወከል ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ እና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፍስሃ ይታገሱ ናቸው፡፡ በስምምነቱ ኢቢሲ አዲስ አበባ ከተማ ሸጎሌ አካባቢ የጀመረውን የዘመናዊ ስቱዲዮ ግንባታ ባንኩ በ200 ሚሊዮን ብር ስፖንሰር ያደረገ ሲሆን፣ ከሚገነቡት ስቱዲዮዎች መካከል ትልቁ የዜና ቻናል ስቱዲዮ ለሚቀጥሉት 10 አመታት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስም የሚጠራ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ የባንኩ የአገልግሎት ማስታወቂያዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ይተላለፋሉ፡፡ የባንካችን ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ በሁለቱ አንጋፋ የሀገራችን ተቋማት መካከል የተመሰረተው ግንኙነት ረጅም ጊዜን ያስቆጠረ መሆኑን አስታውሰው ግንኙነቱ ሲፈለግ የሚጀመርና የሚቋረጥ ሳይሆን፣ ስር የሰደደና ዘላቂ ነው ብለዋል፡፡ የስፖንስርሺፕ ስምምነቱ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ትልቁ ስምምነት እንደሆነም ነው አቶ አቤ የተናገሩት፡፡ አቶ አቤ አያይዘውም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋነኛ ኃላፊነት አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ፣ ስለባንክ አገልግሎት ማስተማርና ከቴክኖሎጂ ጋር ተያይዘው ከሚመጡ የማጭበርበር ድርጊቶች ህብረተሰቡን መከላከል ነው ብለዋል፡፡ እነዚህን ዓላማዎች ከማሳካት አንፃር ኢቢሲ ትልቅ አጋር እንደመሆኑ ይህን የባንኩን ተግባር እንዲደግፍ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ የኢቢሲ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፍስሃ ይታገሱ ባንኩ ለሰጠው አፋጣኝና አዎንታዊ ምላሽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ አያይዘውም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአንድ አንጋፋና መሪ የዘርፉ ተቋም የሚጠበቁ ተግባራትን የሚያከናውን ባንክ መሆኑን አስታውሰው፣ ድርጅታቸው ለጀመረው የለውጥ ርምጃ የሰጠው ምላሽ ይህንኑ አመላካች መሆኑን ገልጸዋል፡፡